በአዲስ አበባ በጥንቃቄ ጉድለት ምክንያት የሚከሰተው የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ እንዳሳሰበው የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን ገለጸ፡፡ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኦፕሬሽን ዘርፍ ሀላፊ ምክትል ኮማንደር አማኑኤል ረዳ እንደገለፁት በዘንድሮው ዓመት ከመስከረም እስከ መጋቢት የተከሰተው የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ከአለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነፃፀር በሰውና በንብረት ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው።
2005 . ከመስከረም እስከ መጋቢት ባሉት 7 ወራት 199 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ሲወድም 5 ሰዎች በእሳት እንዲሁም 27 ሰዎች በድንገተኛ አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል። በቃጠሎ ምክንያት 94 ሰዎች ሲቆስሉ በድንገተኛ አደጋ ምክንያት ደግሞ 4 ሰዎች ተመሳሳይ እጣ ገጥሟቸዋል።
በተመሳሳይ 2006 235 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ሲወድም 8 ሰዎች በእሳት እንዲሁም 50 ሰዎች በድንገተኛ አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል። በእሳት ቃጠሎ 78 ሰዎች፣በድንገተኛ አደጋ ደግሞ 104 ሰዎች የመቁሰል አደጋ ገጥሟቸዋል። እንደ ኮማንደር አማኑኤል ገለፃ በተለይ የድንገተኛ አደጋ ምክንያት ናቸው ካሏቸው መካከል በውሃ መስመጥ፣በአደገኛ እፅ እና በመጠጥ መመረዝ፣በህንፃ ግንባታዎችና በፍርስራሾች እንዲሁም በየመንገዱ ዳር እና የተለያዩ አካባቢዎች ክፍት ሆነው በሚቀመጡ ጉድጓዶች የሚከሰቱ አደጋዎች ተጠቃሾች ናቸው። ብዙ ጊዜ የእሳት አደጋ ሊከሰት የሚችለው በጥንቃቆ ጉድለት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ያሉትንም ዘርዝረዋል። በየጊዜው አየጨመረ የመጣውን የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ለመከላከል የህብረተሰቡ ጥንቃቄ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱም ችግሩን ለመቅረፍና አደጋዎች ሲከሰቱ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል ብለዋል። ተቋሙ በዘንድሮው አመት 8 አዳዲስ የአደጋ መቆጣጠሪያ ተሽከርካሪዎችን የገዛ ሲሆን 140 የአደጋ ተቆጣጣሪ ሰራተኞችንም ቀጥሯል። በአደጋ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ከአደጋው ስፍራ በማውጣት ህይወታቸውን ለማትረፍ እና የሟቾችን አስከሬን ለማውጣት የማሽን ችግር እንደነበር ያስታወሱት የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ማሞ 9 ሚሊዮን ብር የአንድ ማሽን ግዥ ተፈፅሞ ችግሩ መቃለሉን አስረድተዋል። መስሪያ ቤቱ አሁን ያሉትን 7 የአደጋ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ወደ 10 ለማሳደግ በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኝ ሲሆን 33 አምቡላንሶችን በማዘጋጀት 40 ነርሶችንም ቀጥሯል ብለዋል። ለህሙማን፣ ለነፍሰጡሮች እንዲሁም ለማንኛውም ሰብአዊ አገልግሎት ነፃ የአምቡላንስ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑም ህብረተሰቡ ይህንኑ አውቆ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን አሳስበዋል።


0 comments:

Post a Comment

 
Top