- የውጭ ንግድ አገልግሎት ቢሮ በኢትዮጵያ ለመከፈት አቅዳለች
- አጎዋ መራዘሙ እርግጥ ነው ተባለ
አሜሪካ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት በየዓመቱ ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ምርቶች ከኢትዮጵያ እንደምትጠብቅ አስታወቀች፡፡
ለሁለት ቀናት በኢትዮጵያ ቆይታ ያደረጉት የአሜሪካ የንግድ ሚኒስቴር ፔኒ ፕሪትዝከር፣ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በአሜሪካ ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የገበያ ዕድል፣ ማለትም በ‹‹አፍሪካ ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት›› (አጎዋ) አማካይነት ወደ አሜሪካ ከምትልካቸው ምርቶች በዓመት ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ልታገኝ እንደምትችል አስታውቀዋል፡፡  
በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት እያደገ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ እ.ኤ.አ. በ2013 አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የላከቻቸው ምርቶች 92 ሚሊዮን ዶላር እንዳስገኙላትና ከቀዳሚው ዓመት በ24 ከመቶ ዕድገት ማሳየታቸውን አስታውቀዋል፡፡ በሌላ በኩል በዚያው ዓመት ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ከላከቻቸው ምርቶች 111 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ፕሪትዝከር ይፋ አድርገዋል፡፡ 
በጋናና በናይጄሪያ ነዳጅ ላይ ያተኮሩ 20 የአሜሪካ ኩባንያዎች የተካተቱበት ስኬታማ የንግድ ተልዕኮ መምራታቸውንና በርካታ የአሜሪካ ኩባንዎችና ኢንቨስትሮች በአፍሪካ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል፡፡ አሜሪካ በኢትዮጵያ መሰማራት ከምትፈልግባቸው ዘርፎች መካከል አቪዬሽን፣ ኮንስትራክሽን፣ ጤና፣ ግብርናና ኢነርጂ መሆናቸውንም ሚኒስትሯ ይፋ አድርገዋል፡፡ ቦይንግ ኩባንያ ለኢትዮጵያ ትልቁ ኤክስፖርተር እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡ 
የንግድ ሚኒስትሯ ፕሪትዝከር የሁለት ቀናት ጉብኝት ትኩረቱን ያደረገው በአሜሪካ ኩባያዎች የወደፊት የኢንቨስትመንት መስክ ላይ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ለመምከር ታስቦ ቢሆንም፣ ሚኒስትሯና የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ካረን ባስ በወደፊቱ የአጎዋ ላይ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ለመምከር መምጣታቸውን በማስታወቅ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት በኢትዮጵያ አየር መንገድ መሰብሰቢያ ክፍል ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ በኩል የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ብቻ ሲገኙ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪሽያ ሃስላክም ተገኝተዋል፡፡ 
የአሜሪካ የውጭ ንግድ አገልግሎት መስጫ ቢሮ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚከፈትና ለአሜሪካ ኢንቨስትሮች የአገሪቱን ሕግጋትና ሌሎች ጉዳዮች በማጥናት ለኢንቨስትሮች ምክር እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ ከኢትዮጵያ ባሻገር የንግድ አገልግሎት መስጫ ቢሮዎች በአንጎላ፣ በታንዛንያና በሞዛምቢክ ይከፈታሉ ተብሎም ይጠበቃሉ፡፡ ቀደም ሲል በኬንያ፣ በጋና፣ በሞሮኮና በሊቢያ የተከፈቱ ቢሮዎችም ማስፋፊያ እንደሚደረግባቸው፣ ተጨማሪ የአሜሪካ ባለሙያዎችም እንደሚመደቡባቸው ተገልጿል፡፡ 
ከዚህ በሻገር አሜሪካ በአፍሪካ ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ ያደረገችበት የአፍሪካና የአሜሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ፎረም ከአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን በነሐሴ ወር ይካሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የንግድ ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡ ፎረሙ በአሜሪካና በአፍሪካ መካከል ያለውን የፋይናንስ፣ የመሠረተ ልማት፣ የኢነርጂ፣ የግብርና፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ሌሎችንም ግንኙነቶች ያጠናክራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡
የአሜሪካ ኮንግሬስ አባል የሆኑት ካረን ባስ ከሎስ አንጀለስ መምጣታቸውንና በዚያም ‹‹ሊትል ኢትዮጵያ›› ወይም ትንሿ ኢትዮጵያን እንደሚወክሉ ተናግረው ለሁለተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ የተገኙት ግዙፍ፣ መካከለኛና አነስተኛ የአሜሪካ ኩባንያዎች ኢንቨስት ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት ኮንግረሱም እንደሚደግፈው ለማስገንዘብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአሜሪካ ኮንግሬስ እ.ኤ.አ. በ2015 የሚያበቃለትን የአጎዋ ገበያ ለማደስና ለማስቀጠል እየሠራ መሆኑንም ይፋ አድርገዋል፡፡ 
ሆኖም በአሜሪካ የነፃ ገበያ ዕድል ተጠቃሚ መሆን የቻሉት በጣት የሚቆጠሩ የአፍሪካ አገሮች መሆናቸውን አስረድተው፣ ይኸም የሆነው በተለያዩ ችግሮች ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አንዱና ዋናው የመሠረተ ልማት ችግር ነው ያሉት ባስ፣ ለዚህ መፍትሔ ይሆን ዘንድ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ‹‹ፓወር አፍሪካ›› ብለው የሰየሙት አዲሱ የአሜሪካ የኃይል አቅርቦት ተነሳሽነት ነው፡፡ በርካታ አፍሪካውያን የኤሌክትሪክ ኃይል አግልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ታስቦ የተነደፈው ‹‹ፓወር አፍሪካ›› ፕሮግራም፣ በኢትዮጵያ የጂኦተርማልና የሶላር ኃይል ምንጮች ላይ የሚያተኩር እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ 
አሜሪካ አጎዋን ማስቀጠሏ እርግጥ መሆኑ ግልጽ ቢደረግም፣ አፍሪካውያን የአሜሪካ ደረጃን በጠበቀ ሁኔታ ምርቶቻቸውን እንዲያመርቱና እንዲልኩ ማድረግ የሚጠበቅ መሆኑን የኮንግረስ አባሏ ይፋ አድርገዋል፡፡ የአፍሪካ ዲፕሎማቶች ከአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ጋር የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነቱን ለማጠናከር ንግግር በማድረግ ላይ እንደሚገኙም ተነግሯል፡፡ 
አሜሪካውያን በቻይና፣ በህንድና በሌሎች የእስያ አገሮች አፍሪካ ውስጥ የተወሰደባቸውን የንግድ የበላይነት በሚመለከት ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው ሚኒስትሯ፣ በርካታ ኩባንያዎች ወደ አፍሪካ ለመምጣት ፍላጎት እንዳላቸው፣ ሬይክያቪክ የተባለውን የጂኦተርማል የግል ኩባንያ ጨምሮ ጄኔራል ኤሌክትሪክ፣ ቦይንግ፣ ማይክሮ ሶፍትና ሌሎችም ኩባንያዎች በአፍሪካ ውስጥ ያላቸውን ስኬታማ ሚና ጠቅሰዋል፡፡ ድንበር ተሻጋሪ ኩባንያዎችን በሚመለከት ጥያቄ የቀረበላቸው ሚኒስትሯ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ያስቀመጠው ስትራቴጂ ቢኖርም፣ በፋይናንስና በመሠረተ ልማት መስኮች ላይ መሥራት እንደሚጠበቅ፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፍም መፃኢ ዕድል የሚታይበት መስክ መሆኑን ሚኒስትሯ በምላሻቸው አስረድተዋል፡፡

0 comments:

Post a Comment

 
Top